2 ሳሙኤል 23:11-17 NASV

11 ከእርሱም ቀጥሎ የአሮዳዊው የአጌ ልጅ ሣማ ነበር፤ ፍልስጥኤማውያንም ሌሒ በተባለ ስፍራ ምስር በሞላበት አንድ ዕርሻ ላይ፣ በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ፣ የእስራኤል ሰራዊት ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤

12 ሣማ ግን የቆመበትን ስፍራ አለቀቀም፤ ጦርነቱንም ተቋቁሞ ፍልስጥኤማውያንን ገደለ፤ በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር ታላቅ ድል ሰጠ።

13 በመከር ወራት፣ የፍልስጥኤም ሰራዊት በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ሳለ፣ ከሠላሳዎቹ አለቆች ሦስቱ ዳዊት ወዳለበት ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ።

14 በዚያም ጊዜ ዳዊት በምሽግ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ሰራዊት በቤተልሔም ነበረ፤

15 ዳዊትም በናፍቆት፣ “በቤተልሔም በር አጠገብ ካለችው ጒድጓድ ውሃ ማን ባመጣልኝ!” አለ።

16 ስለዚህ ሦስቱ ኀያላን በፍልስጥኤማውያን ሰራዊት መካከል ሰንጥቀው በማለፍ፣ በቤተልሔም በር አጠገብ ካለችው ጒድጓድ ውሃ ቀድተው ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን አልጠጣውም፤ ይልቁን በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አድርጎ አፈሰሰው፤

17 “እርሱም፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲህ ያለውን ነገር ላርግ? ይህስ ከእኔ ይራቅ! ይህ በነፍሳቸው ቈርጠው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን?” አለ፤ ዳዊትም ሊጠጣው አልፈለገም። እንግዲህ ሦስቱ ኀያላን ሰዎች ያደረጉት ጀብዱ እንዲህ ነበር።