3 የእስራኤል አምላክ ተናገረ፤የእስራኤልም ዐለት እንዲህ አለኝ፤ሰዎችን በጽድቅ የሚገዛ፣በፈሪሀ እግዚአብሔርም የሚያስተዳድር፣
4 እርሱ፣ ደመና በሌለበት፣ በማለዳ ፀሓይ በምትወጣበት ጊዜ፣እንዳለው ብርሃን ነው፤በምድር ላይ ሣርን እንደሚያበቅለው፣ከዝናብም በኋላ እንዳለው የብርሃን ጸዳል ነው።’
5 “የእኔስ ቤት በእግዚአብሔር ዘንድ ትክክል አይደለምን?ሁሉንም ነገር አዘጋጅቶና ጠብቆ፣ከእኔ ጋር ዘላለማዊ ኪዳን ያደረገ አይደለምን?ድነቴን ከፍጻሜ የሚያደርሰው፣መሻቴን ሁሉ የሚሰጠኝ እርሱ አይደለምን?
6 ነገር ግን ክፉ ሰዎች ሁሉ፣በእጅ እንደማይሰበሰብ እንደ እሾኽ ይጣላሉ።
7 እሾኽ የሚነካ ሁሉ፣የብረት መሣሪያ ወይም የጦር ዘንግ ይይዛል፤ባሉበትም ቦታ ፈጽመው በእሳት ይቃጠላሉ።
8 የዳዊት ኀያላን ሰዎች ስም የሚከተለው ነው፤ የታሕክሞን ሰው ዮሴብ በሴትቤት የሦስቱ አለቆች አለቃ ሲሆን፣ እርሱም ጦሩን ሰብቆ በአንድ ውጊያ ላይ ስምንት መቶ ሰው የገደለ ነው።
9 ከእርሱ ቀጥሎ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ ኤልዔዘር ነበረ፤ እርሱም ለጦርነት አንድ ላይ ተሰብስበው የነበሩትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ፣ ከዳዊት ጋር ከነበሩት ከሦስቱ ኀያላን ሰዎች አንዱ ነበር። ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ሸሹ።