2 ሳሙኤል 23:8-14 NASV

8 የዳዊት ኀያላን ሰዎች ስም የሚከተለው ነው፤ የታሕክሞን ሰው ዮሴብ በሴትቤት የሦስቱ አለቆች አለቃ ሲሆን፣ እርሱም ጦሩን ሰብቆ በአንድ ውጊያ ላይ ስምንት መቶ ሰው የገደለ ነው።

9 ከእርሱ ቀጥሎ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ ኤልዔዘር ነበረ፤ እርሱም ለጦርነት አንድ ላይ ተሰብስበው የነበሩትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ፣ ከዳዊት ጋር ከነበሩት ከሦስቱ ኀያላን ሰዎች አንዱ ነበር። ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ሸሹ።

10 እርሱ ግን የቆመበትን ስፍራ አለቀቀም፤ እጁ እስኪዝልና ከሰይፉ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን ወጋ፤ በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር ታላቅ ድልን ሰጠ። የሸሸውም ሰራዊት ወደ ኤልዔዘር የተመለሰው የተገደሉትን ሰዎች ለመግፈፍ ብቻ ነበር።

11 ከእርሱም ቀጥሎ የአሮዳዊው የአጌ ልጅ ሣማ ነበር፤ ፍልስጥኤማውያንም ሌሒ በተባለ ስፍራ ምስር በሞላበት አንድ ዕርሻ ላይ፣ በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ፣ የእስራኤል ሰራዊት ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤

12 ሣማ ግን የቆመበትን ስፍራ አለቀቀም፤ ጦርነቱንም ተቋቁሞ ፍልስጥኤማውያንን ገደለ፤ በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር ታላቅ ድል ሰጠ።

13 በመከር ወራት፣ የፍልስጥኤም ሰራዊት በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ሳለ፣ ከሠላሳዎቹ አለቆች ሦስቱ ዳዊት ወዳለበት ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ።

14 በዚያም ጊዜ ዳዊት በምሽግ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ሰራዊት በቤተልሔም ነበረ፤