2 ሳሙኤል 24:1-7 NASV

1 እንደ ገናም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ዳዊትንም በእነርሱ ላይ በማስነሣት፣ “ሂድ እስራኤልንና ይሁዳን ቊጠር” አለው።

2 ስለዚህም ንጉሡ ኢዮአብንና አብረውት ያሉትን የጦር አዛዦች፣ “ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ወዳሉት የእስራኤል ነገዶች ሁሉ ሂዱ፤ ብዛታቸው ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ እንድችልም ተዋጊዎቹን መዝግቡ” አላቸው።

3 ኢዮአብ ግን ንጉሡን፣ “አምላክህ እግዚአብሔር ሰራዊቱን መቶ ዕጥፍ ያድርገው፤ የጌታዬ የንጉሡ ዐይን ይህን ለማየት ይብቃ፤ ንጉሡ ጌታዬ ግን ይህን ለማድረግ የፈለገው ለምንድን ነው?” ሲል መለሰለት።

4 ሆኖም የንጉሡ ቃል ኢዮአብንና የሰራዊቱን አዛዦች ስላሸነፋቸው፣ የእስራኤልን ሰራዊት ለመመዝገብ ከፊቱ ወጥተው ሄዱ።

5 ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ፣ በሸለቆው ውስጥ ካለችው ከተማ በስተ ደቡብ በምትገኘው በአሮዔር አጠገብ ሰፈሩ፤ ከዚያም በጋድ በኩል አድርገው ወደ ኢያዜር ሄዱ፤

6 እንዲሁም ወደ ገለዓድና ወደተባሶን አዳሰይ፣ ቀጥሎም ወደ ዳንየዓን ከዚያም ዞረው ወደ ሲዶና ሄዱ።

7 ደግሞም ወደ ጢሮስ ምሽግ፣ ወደ ኤዊያውያንና ወደ ከነዓናውያን ከተሞች፣ በመጨረሻም በይሁዳ ደቡብ ወዳለችው ወደ ቤርሳቤህ ሄዱ።