2 ሳሙኤል 24:16-22 NASV

16 የእግዚአብሔር መልአክ ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት እጁን በዘረጋ ጊዜ፣ የደረሰው ጒዳት እግዚአብሔርን ስላሳዘነው፣ ሕዝቡን የሚቀሥፈውን መልአክ “በቃ! እጅህን መልስ” አለው። በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር።

17 ዳዊት ሕዝቡን የሚቀሥፈውን መልአክ ባየ ጊዜ እግዚአብሔርን፣ “እነሆ ኀጢአት የሠራሁም የተሳሳትሁም እኔ ነኝ፤ እነዚህ ግን በጎች ናቸው፤ ምን አጠፉ? እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን” አለ።

18 በዚያን ቀን ጋድ ወደ ዳዊት ዘንድ ሄዶ፣ “ውጣና በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሥራ” አለው።

19 ስለዚህ ዳዊት፣ እግዚአብሔር በጋድ በኩል ባዘዘው መሠረት ወጣ።

20 ኦርናም ቍልቍል ሲመለከት፣ ንጉሡና ሰዎቹ ወደ እርሱ ሲመጡ አየ፤ ከዚያም ወጥቶ ወደ መሬት ለጥ ብሎ ለንጉሡ እጅ ነሣ።

21 ኦርናም፣ “ንጉሥ ጌታዬ ወደ አገልጋዩ የመጣው ለምንድን ነው?” አለ።ዳዊትም መልሶ፣ “መቅሠፍቱ ከሕዝቡ እንዲከለከል ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንድሠራ ዐውድማህን ልገዛ ነው” አለው።

22 ኦርናም ዳዊትን እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ጌታዬ ደስ ያለውን ወስዶ መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሬዎች አሉ፤ ለሚነደውም ዕንጨት፣ የመውቂያው ዕቃና የበሬ ቀንበር አለ።