1 በዳዊት ቤትና በሳኦል ቤት መካከል የነበረው ጦርነት ብዙ ጊዜ ቈየ፤ ዳዊት እየበረታ ሲሄድ፣ የሳኦል ቤት ግን እየተዳከመ መጣ።
2 ዳዊት በኬብሮን ሳለ፣ ስድስት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤የበኵር ልጁ፣ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆም የተወለደው አምኖን፣
3 ሁለተኛው፣ የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ የተወለደው ኪልአብ፣ ሦስተኛው፣ ተልማይ ከተባለው ከጌሹር ንጉሥ ልጅ ከመዓካ የተወለደው አቤሴሎም፣
4 አራተኛው፣ ከአጊት የተወለደው አዶንያስ፤ አምስተኛው፣ ከአቢጣል የተወለደው ሰፋጥያ፣
5 ስድስተኛው፣ ከዳዊት ሚስት ከዔግላ የተወለደው ይትረኃም ነበር፤ እነዚህ ዳዊት በኬብሮን ሳለ የተወለዱለት ናቸው።
6 የሳኦል ቤትና የዳዊት ቤት በጦርነት ላይ በነበሩበት ጊዜ፣ አበኔር በሳኦል ቤት ላይ ኀይሉን ያጠናክር ነበር።
7 ሳኦልም የኢዮሄልን ልጅ ሪጽፋን በቁባትነት አስቀምጦአት ነበር፤ ኢያቡስቴም አበኔርን፣ “ለምንድን ነው ከአባቴ ቁባት ጋር የተኛኸው?” አለው።