መሳፍንት
ምዕራፎች 13:6-12
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
6ከዚያም ሴቲቱ ወደ ባሏ ሄዳ እንዲህ አለችው፤ “የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፤ የእግዚአብሔር መልአክ የሚመስልና እጅግ የሚያስደነግጥ ነበር። ከየት እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፤ እርሱም ስሙን አልነገረኝም፤
7ነገር ግን፣ ‘ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ ርኵስ ነገር አትብዪ፤ ልጁም ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናልና’ ብሎኛል።”
8ከዚያም ማኑሄ፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚወለደውን ልጅ እንዴት አድርገን ማሳደግ አንዳለብን እንዲያስተምረን ያ ወደ እኛ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እንደ ገና እንዲመጣ ታደርግ ዘንድ እለምንሃለሁ”። ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።
9እግዚአብሔርም የማኑሄን ጸሎት ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሴቲቱ በዕርሻ ውስጥ ሳለች ተገለጠላት፤ በዚህ ጊዜ ግን ባሏ ማኑሄ አብሮአት አልነበረም።
10እርሷም ለባሏ ለመንገር ፈጥና በመሄድ፣ “ባለፈው ጊዜ የተገለጠልኝ ሰው ዛሬም ተገለጠልኝ” አለችው።
11ማኑሄም ተነሥቶ ሚስቱን ተከተላት፤ ሰውየው እንደ ደረሰም፣ “ከሚስቴ ጋር ተነጋግረህ የነበርኸው አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፤ “አዎን እኔ ነኝ” አለው።
12ማኑሄም፣ “ያልኸው በሚፈጸምበት ጊዜ የልጁ ሕይወት የሚመራው እንዴት ነው? እኛስ ምን ማድረግ አለብን?” ሲል ጠየቀው።