መሳፍንት 14:11-17 NASV

11 እርሱም ለፍልስጥኤማውያን በታየ ጊዜ፣ ሠላሳ አጃቢዎች ሰጡት።

12 ሳምሶን እንዲህ አላቸው፤ አንድ እንቈቅልሽ እነግራችኋለሁ፤ ታዲያ ፍቺውን በሰርጉ በዓል ሰባት ቀኖች ውስጥ ከሰጣችሁኝ፣ ሠላሳ የቀጭን ፈትል በፍታ ቀሚስና ሠላሳ የክት ልብስ እሰጣችኋለሁ።

13 እንቈቅልሹን ካልፈታችሁልኝ ግን ሠላሳ የቀጭን ፈትል በፍታ ቀሚስና ሠላሳውን የክት ልብስ እናንተ ትሰጡኛላችሁ።”እነርሱም፣ “በል እንቈቅልሽህን ንገረንና እንስማው” አሉት።

14 ሳምሶንም፣“ከበላተኛው መብል፣ከብርቱም ጣፋጭ ነገር ወጣ” አላቸው።እነርሱም እስከ ሦስት ቀን ድረስ እንቈቅልሹን መፍታት አልቻሉም ነበር።

15 በአራተኛው ቀን የሳምሶንን ሚስት፣ “የእንቈቅልሹን ፍች እንዲነግረን ባልሽን እስቲ አግባቢልን፤ ያለዚያ አንቺንም የአባትሽንም ቤተ ሰብ በእሳት እናቃጥላችኋለን፤ ጠርታችሁ የጋበዛችሁን ልትዘርፉን ነው?” አሏት።

16 ከዚያ የሳምሶን ሚስት ተንሰቅስቃ እያለቀሰች ከፊቱ በመቅረብ፣ “ለካስ ትጠላኛለህ! በእርግጥ አትወደኝም” አለችው።እርሱም፣ “ይህን ለአባቴም ሆነ ለእናቴ አልነገርኋቸውም፤ ታዲያ ለአንቺ ለምን እነግርሻለሁ?” አላት።

17 ሚስቱም በሰርጉ በዓል ሰባት ቀን ሙሉ እያለቀሰች ጨቀጨቀችው፤ አጥብቃ ስለ ነዘነዘችውም በመጨረሻ በሰባተኛው ቀን ነገራት፤ እርሷም በበኩሏ የእንቈቅልሹን ፍች ለሕዝቧ ነገረች።