መሳፍንት 15:12-18 NASV

12 እነርሱም፣ “አስረን ለፍልስጥኤማውያን ልንሰጥህ ይኸው መጥተናል” አሉት።ሳምሶንም፣ “እናንተ ራሳችሁ ላትገድሉኝ ማሉልኝ” አላቸው።

13 እነርሱም፣ “አስረን ብቻ ለእነርሱ አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ ራሳችን አንገድልህም” አሉት፤ ከዚያ በሁለት አዳዲስ ገመድ አስረው ከዐለቱ ዋሻ አወጡት።

14 ሳምሶን ሌሒ እንደ ደረሰም ፍልስጥኤማውያን እየጮኹ ወደ እርሱ መጡ፤ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳምሶን ላይ በኀይል ወረደበት። እጆቹ የታሰሩበትም ገመድ እሳት ውስጥ እንደ ገባ የተልባ እግር ፈትል ሆኖ ከእጆቹ ላይ ወደቀ።

15 ከዚያም በቅርቡ የሞተ የአንድ የአህያ መንጋጋ አይቶ ከመሬት አነሣ፤ በዚያም አንድ ሺህ ሰው ገደለ።

16 ሳምሶንም፣“በአንድ የአህያ መንጋጋ፣ሺህ ሰው ዘራሪ፤በአንድ የአህያ መንጋጋ፣ሺህ ሬሳ አነባባሪ፡ ብሎ ፎከረ።

17 ይህን ተናግሮ እንዳበቃ የአህያውን መንጋጋ ከእጁ ወዲያ ወረወረው፤ የዚያም ቦታ ስም ራማት ሌሒ ተብሎ ተጠራ።

18 እጅግ ተጠምቶ ስለ ነበር፤ “እነሆ፤ ለአገልጋይህ ይህን ታላቅ ድል አጐናጽፈሃል፤ ታዲያ አሁን በውሃ ጥም ልሙት? እንዴትስ በእነዚህ ባልተገረዙ ፍልስጥኤማውያን እጅ ልውደቅ? በማለት ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።