መሳፍንት 16:17-23 NASV

17 ስለዚህ ሁሉንም ነገር ነገራት፤ እንዲህም አለ፤ “ከተወለድሁ ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየሁ ስለ ሆንሁ ራሴን ምላጭ ነክቶት አያውቅም፤ የራሴ ጠጒር ቢላጭ ግን ኀይሌ ተለይቶኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት።

18 ደሊላ ሁሉንም ነገር እንደ ነገራት በተረዳች ጊዜ፣ ለፍልስጥኤማውያን ገዦች “ሁሉንም ነገር ነግሮኛልና ተመልሳችሁ ኑ” ብላ ላከችባቸው፤ የፍልስጥኤማውያን ገዦችም ብሩን ይዘው ተመልሰው መጡ።

19 ደሊላ፣ ሳምሶንን በጭኗ ላይ አስተኝታ እንቅልፍ እንዲወስደው ካደረገች በኋላ አንድ ሰው ጠርታ ሰባቱን የጠጒር ቈንዳላዎቹን አስላጨቻቸው፤ እርሷም ታስጨንቀው ጀመር፤ ኀይሉም ተለየው።

20 እርሷም፣ “ሳምሶን፤ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” አለችው።ሳምሶን ከእንቅልፉ ነቅቶ፣ “እንደ ወትሮው አደርጋለሁ” አለ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ ተወው አላወቀም ነበር።

21 ከዚያም ፍልስጥኤማውያን ያዙት፤ ዐይኖቹን አውጥተው ወደ ጋዛ ይዘውት ወረዱ፤ በናስ ሰንሰለት አስረውም እስር ቤት ውስጥ እህል እንዲፈጭ አደረጉት፤

22 ነገር ግን ከተላጨ በኋላ ጠጒሩ እንደ ገና ማደግ ጀመረ።

23 በዚህ ጊዜ የፍልስጥኤማውያን ገዦች፣ “አምላካችን ዳጎን፣ ጠላታችን ሳምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል” ብለው በመደሰት ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ለማቅረብ ተሰበሰቡ።