ዘሌዋውያን 10:15-20 NASV

15 የቀረበውን ወርችና የተወዘወዘውን ፍርምባ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የመወዝወዝ መሥዋዕት ሆኖ በእሳት ከቀረበው ሥብ ጋር ይምጣ። ይህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት ለአንተና ለልጆችህ ለዘላለም የተመደበ ድርሻ ይሆናል።”

16 ሙሴ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚቀርበውን ፍየል አጥብቆ ፈለገ፤ መቃጠሉንም በተረዳ ጊዜ የተረፉትን የአሮንን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን ተቈጣቸው፤ እንዲህም አላቸው፤

17 “የኀጢአት መሥዋዕቱን ለምን በተቀደሰው ስፍራ አልበላችሁትም? እጅግ የተቀደሰ ነው፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ስርየት በማስገኘት የሕዝቡን ኀጢአት እንድታስወግዱበት የተሰጣችሁ ነበር፤

18 ደሙ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ስላልገባ፣ በሰጠሁት ትእዛዝ መሠረት ፍየሉን በተቀደሰው ስፍራ መብላት ይገባችሁ ነበር።”

19 አሮንም ሙሴን፣ “እነሆ፤ በዛሬው ቀን የኀጢአት መሥዋዕታቸውንና የሚቃጠል መሥዋዕታቸውን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቀረቡ፤ እኔም እንዲህ ያለ ነገር የደረሰብኝ ሰው ነኝ፤ ታዲያ፣ ዛሬ የኀጢአት መሥዋዕቱን ብበላ ኖሮ እግዚአብሔርስ (ያህዌ) ደስ ይለው ኖሮአልን?” አለው።

20 ሙሴም ይህን በሰማ ጊዜ መልሱ አረካው።