ዘሌዋውያን 10:9-15 NASV

9 “እንዳትሞቱ አንተና ልጆችህ ወደ መገናኛው ድንኳን በምትገቡበት ጊዜ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጡ፤ ይህም በልጅ ልጃችሁ ዘንድ የሚጠበቅ ዘላለማዊ ሥርዐት ነው።

10 የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን፣ ርኵሱንና ንጹሑን ለዩ፤

11 እግዚአብሔርም (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት የሰጣቸውን ሥርዐት ሁሉ ለእስራኤላውያን አስተምሩ።

12 ሙሴም አሮንንና የተረፉትን ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፤ “በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከቀረበው የእህል ቊርባን የቀረውን ወስዳችሁ ያለ እርሾ ጋግሩት፤ እጅግ ቅዱስ ስለ ሆነ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት፤

13 ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርበው መሥዋዕት ያንተና የልጆችህ ድርሻ ይህ ስለ ሆነ፣ በተቀደሰ ስፍራ ብሉት፤ እንዲህ ታዝዣለሁና።

14 ከእስራኤላውያን የኅብረት መሥዋዕት ላይ የእናንተ ድርሻ ሆኖ ስለተሰጠ፣ የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ በሆነ ስፍራ ብሉት።

15 የቀረበውን ወርችና የተወዘወዘውን ፍርምባ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የመወዝወዝ መሥዋዕት ሆኖ በእሳት ከቀረበው ሥብ ጋር ይምጣ። ይህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት ለአንተና ለልጆችህ ለዘላለም የተመደበ ድርሻ ይሆናል።”