ዘሌዋውያን 12:3-8 NASV

3 ሕፃኑም በስምንተኛው ቀን ይገረዝ።

4 ሴትዮዋም ከደሟ እስክትነጻ ድረስ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቆይ፤ የመንጻቷም ወራት እስኪፈጸም ድረስ ማንኛውንም የተቀደሰ ነገር አትንካ፤ ወደ ቤተ መቅደስም አትግባ።

5 ነገር ግን የወለደችው ሴት ልጅ ከሆነ፣ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ ሁለት ሳምንት ትረክሳለች፤ ከዚያም ከደሟ እስክትነጻ ስድሳ ስድስት ቀን ትቆይ።

6 “ ‘ሴትዮዋ ወንድ ወይም ሴት ልጅዋን ወልዳ የመንጻትዋ ጊዜ ሲፈጸም፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት የአንድ ዓመት ጠቦት፣ ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ የዋኖስ ጫጩት ወይም አንድ ርግብ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወስዳ ካህኑ ዘንድ ታቅርብ።

7 ካህኑም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርበው፤ ያስተሰርይላትም፤ ሴትዮዋም ከደሟ ፈሳሽ ትነጻለች።“ ‘ሴትዮዋ ወንድ ወይም ሴት ብትወልድ ሕጉ ይኸው ነው።

8 ጠቦት ለማምጣት ዐቅምዋ ካልፈቀደ፣ ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች፣ አንዱ ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ ሌላው ደግሞ ለኀጢአት መሥዋዕት ታቅርብ፤ በዚህም ካህኑ ያስተሰር ይላታል፤ እርሷም ትነጻለች።’ ”