ዘሌዋውያን 15:13-19 NASV

13 “ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው ከፈሳሹ ሲነጻ፣ በሕጉ መሠረት ለመንጻቱ ሰባት ቀን ይቊጠር፤ ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በምንጭ ውሃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል።

14 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ይዞ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በመቅረብ ለካህኑ ይስጥ።

15 ካህኑም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ በዚህ መሠረት ስለ ፈሳሹ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለሰውየው ያስተሰርይለታል።

16 “ ‘አንድ ሰው ዘሩ በሚፈስበት ጊዜ ሰውነቱን በሙሉ በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል።

17 የፈሰሰው ዘር የነካው ማንኛውም ልብስ ወይም ቊርበት በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል።

18 አንድ ሰው ከአንዲት ሴት ጋር ግብረ ሥጋ ፈጽሞ ዘር ቢፈሰው፣ ሁለቱም በውሃ ይታጠቡ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩሳን ይሆናሉ።

19 “ ‘ሴት ጊዜውን እየጠበቀ የሚመጣው የደም መፍሰስ ቢኖርባት፣ የወር አበባዋ ርኵሰት እስከ ሰባት ቀን ይቆያል፤ በዚህ ጊዜ ማንም ሰው ቢነካት እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።