ዘሌዋውያን 20:17-23 NASV

17 “ ‘አንድ ሰው የአባቱ ወይም የእናቱ ልጅ የሆነችውን እኅቱን አግብቶ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ አድራጎቱ አሳፋሪ ነው፤ በሕዝባቸው ፊት ከሕዝባቸው ተለይተው ይጥፉ። ሰውየው እኅቱን አዋርዶአልና ይጠየቅበታል።

18 “ ‘ማንኛውም ሰው በወር አበባዋ ጊዜ ከሴት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ የፈሳሿን ምንጭ ገልጦአልና፣ እርሷም የፈሳሿን ምንጭ ገልጣለችና፣ ሁለቱም ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ።

19 “ ‘ከእናትህም ሆነ ከአባትህ እኅት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ የሥጋ ዝምድናን ማቃለል ስለ ሆነ ሁለታችሁም ትጠየቁበታላችሁ።

20 “ ‘ማንኛውም ሰው ከአጎቱ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ አጎቱን አዋርዶአልና ሁለቱም ይጠየቁበታል፤ ያለ ልጅም ይሞታሉ።

21 “ ‘ማንኛውም ሰው የወንድሙን ሚስት ቢያገባ አድራጐቱ ርኵሰት ነው፤ ወንድሙን አዋርዶአልና፣ ያለ ልጅም ይቀራሉ።

22 “ ‘እንድትኖሩባት እናንተን የማስገባባት ምድር እንዳትተፋችሁ ሥርዐቴንና ሕጌን ጠብቁ፤ አድርጉም።

23 ከፊታችሁ የማሳድዳቸውን አሕዛብ ልማድ አትከተሉ፤ እነዚህን ሁሉ በማድረጋቸው ተጸየፍኋቸው።