9 ኅብስቱ የአሮንና የልጆቹ ድርሻ ነው፤ በተቀደሰ ስፍራም ይበሉታል፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርበው መሥዋዕት እጅግ የተቀደሰ ድርሻቸው ነውና።”
10 እናቱ እስራኤላዊት፣ አባቱ ግብፃዊ የሆነ አንድ ሰው በእስራኤላውያን መካከል ወጣ፤ በሰፈርም ውስጥ ከአንድ እስራኤላዊ ጋር ተጣሉ።
11 የእስራኤላዊቱ ልጅ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም በማቃለል ሰደበ፤ ስለዚህም ወደ ሙሴ አመጡት፤ የሰውየው እናት ስም ሰሎሚት ነበር፤ እርሷም ከዳን ወገን የተወለደው የደብራይ ልጅ ነበረች።
12 የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፈቃድም ግልጽ እስኪሆንላቸው ድረስ በግዞት አኖሩት።
13 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
14 “ተሳዳቢውን ከሰፈር ወደ ውጭ አውጣው፤ ሲሳደብ የሰሙት ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ በድንጋይ ይውገረው።
15 እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ማንም ሰው አምላኩን (ኤሎሂም) ቢሳደብ ኀጢአት ሠርቶአልና ይጠየቅበታል።