ዘሌዋውያን 27:22-28 NASV

22 “ ‘አንድ ሰው የወረሰው ርስት ያልሆነውን፣ በገንዘቡ የገዛውን የዕርሻ መሬት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ቢቀድስ፣

23 ካህኑ የእርሻውን መሬት ዋጋ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ባለው ጊዜ መጠን ይተምናል፤ ሰውየው የተተመነውን ዋጋ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ አድርጎ በዚያኑ ዕለት ይክፈል።

24 በኢዮቤልዩ ዓመትም የዕርሻው መሬት የቀድሞው ባለ ርስት ለነበረው፣ ለሸጠውም ሰው ይመለሳል።

25 እያንዳንዱ ዋጋ የሚተመነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ ሆኖ አንዱ ሰቅል ሃያ ጌራ ነው።

26 “ ‘የእንስሳት በኵር ቀድሞውኑ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ ሆነ፣ ማንም ሰው የእንስሳትን በኵር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መቀደስ አይችልም፤ በሬም ሆነ በግ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ነውና።

27 እንስሳው ርኩስ ከሆነ ግን፣ ባለቤቱ በተተመነው ዋጋ ላይ አንድ አምስተኛ ጨምሮ ሊዋጀው ይችላል፤ የማይዋጀው ከሆነ ግን በተተመነው ዋጋ ይሸጥ።

28 “ ‘ነገር ግን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ተለይቶ የተሰጠ ማንኛውም ነገር፦ ሰውም ሆነ እንስሳ ወይም በውርስ የተገኘ መሬት አይሸጥም፤ አይዋጅምም። ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠ ማንኛውም ነገር እጅግ የተቀደሰ ነውና።