8 ስእለት የተሳለው ድኻ ከሆነና ግምቱን መክፈል ካልቻለ ግን፣ ለስጦታ ያሰበውን ሰው ወደ ካህኑ ያምጣ፤ ካህኑም የተሳለው ሰው ባለው ዐቅም መሠረት መክፈል የሚገባውን ይተምንለታል።
9 “ ‘ሰውየው የተሳለው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ የሚችል እንስሳ ከሆነ፣ እንዲህ ያለው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠ እንስሳ የተቀደሰ ይሆናል።
10 ሰውየው መልካም የሆነውን እንስሳ መልካም ባልሆነው፣ መልካም ያልሆነውንም መልካም በሆነው አይለውጥ ወይም አይተካ፤ አንዱን እንስሳ በሌላው ከተካም ሁለቱ የተቀደሱ ይሆናሉ።
11 እንስሳው በሥርዐቱ መሠረት የረከሰ፣ ለእግዚአብሔርም (ያህዌ) መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ የማይገባው ከሆነ፣ ሰውየው እንስሳውን ወደ ካህኑ ያቅርብ፤
12 መልካም ቢሆን ወይም ባይሆን፣ ካህኑ ዋጋውን ይወስን፤ የካህኑም ውሳኔ የጸና ይሆናል።
13 ባለቤቱ እንስሳውን መዋጀት ከፈለገ ግን፣ በተተመነው ዋጋ ላይ አንድ አምስተኛ መጨመር አለበት።
14 “ ‘አንድ ሰው ቤቱን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ይሆን ዘንድ ቢቀድስ፣ መልካም ቢሆን ወይም ባይሆን ካህኑ ዋጋውን ይተምን፤ ካህኑም የተመነው ዋጋ የጸና ይሆናል።