1 “ ‘አንድ ሰው ስላየውና ስለሚያውቀው ነገር ሕጋዊ ምስክርነቱን እንዲሰጥ ተጠይቆ ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆን፣ ይህ ሰው ኀጢአት ሠርቶአልና ይጠየቅበታል።
2 “ ‘ማንኛውም ሰው ሳያውቅ በሥርዐቱ መሠረት የተከለከለውን ርኩስ ነገር ቢነካ፣ ይኸውም፦ የረከሰ የአውሬ በድን ወይም የረከሰ የቤት እንስሳ በድን ወይም በደረቱ እየተሳበ የሚንቀሳቀሰውን የረከሰ ፍጥረት በድን ቢነካ ይህ ሰው ረክሶአል፤ በደለኛም ነው።
3 “ ‘ወይም የሰውን ርኵሰት ይኸውም ርኵስ የሚያደርገውን ማናቸውንም ነገር ሳያውቅ ቢነካ፣ ነገሩን ባወቀ ጊዜ በደለኛ ይሆናል።
4 “ ‘ሰዎች በሚምሉበት በማናቸውም ነገር፣ በጎ ወይም ክፉ ለማድረግ ሳያስብ በግዴለሽነት ቢምል በኋላ ግን ነገሩን ባወቀ ጊዜ በደለኛ ይሆናል።