1 በስምንተኛውም ቀን ሙሴ አሮንንና ልጆቹን እንዲሁም የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠራቸው፤
2 አሮንንም እንዲህ አለው፤ “የኀጢአት መሥዋዕት እንዲሆንልህ አንድ እንቦሳ እንዲሁም የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲሆንልህ አንድ አውራ በግ፣ ወስደህ፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቅርባቸው፤ ሁለቱም እንከን የሌለባቸው ይሁኑ።
3 እስራኤላውያንንም እንዲህ በላቸው፤ ‘ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት እንከን የሌለባቸውን የአንድ ዓመት እምቦሳና የአንድ ዓመት ጠቦት፣
4 ለኅብረት መሥዋዕት አንድ በሬና አንድ አውራ በግ በዘይት ከተለወሰ የእህል ቊርባን ጋር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለመሠዋት አቅርቡ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዛሬ ይገለጥላችኋልና።’ ”
5 እነርሱም ሙሴ ያዘዛቸውን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አመጡ፤ ሕዝቡም በሙሉ ቀርበው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቆሙ።