1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2 “ከተቀጠቀጠ ብር ሁለት መለከት አብጅ፤ ማኅበረ ሰቡን ለመጥሪያና ከሰፈራቸው እንዲነሡም ለመቀስቀሻ አድርጋቸው።
3 ሁለቱ መለከቶች ሲነፉ ማኅበረ ሰቡ በሙሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አንተ ዘንድ ይሰብሰብ፤
4 ነገር ግን አንዱ መለከት ብቻ ከተነፋ አለቆች ማለት የእስራኤል ጐሣ መሪዎች አንተ ዘንድ ይሰብሰቡ፤
5 መለከቱ ከፍ ባለ ድምፅ ሲነፋ በስተ ምሥራቅ የሰፈሩት ነገዶች ጒዞ ይጀምሩ፤
6 መለከቱ ከፍ ባለ ድምፅ ለሁለተኛ ጊዜ ሲነፋ በስተ ደቡብ የሰፈሩት ነገዶች ጒዞ ይጀምሩ፤ ከፍ ያለው ድምፅ ጒዞ ለመጀመር ምልክት ይሆናል።
7 ማኅበሩን ለመሰብሰብ መለከቶች ይነፉ፤ ነገር ግን ድምፁ አይጩኽ።