ዘኁልቍ 23:1-7 NASV

1 በለዓም፣ “እዚህ ሰባት መሠዊያ ሥራልኝ፤ ሰባት ኮርማዎችና ሰባት አውራ በጎችም አዘጋጅልኝ” አለው።

2 ባላቅም በለዓም እንደ ነገረው አደረገ፤ ሁለቱም በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ ኮርማና አንድ አውራ በግ አቀረቡ።

3 ከዚያም በለዓም ባላቅን፣ “እኔ ወደዚያ ስሄድ፣ አንተ እዚሁ መሥዋዕትህ አጠገብ ቈይ፤ ምናልባትም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሊገናኘኝ ይመጣ ይሆናል፤ የሚገልጥልኝንም ሁሉ እነግርሃለሁ” አለው። ከዚያም በለዓም ወደ አንድ ገላጣ ኰረብታ ሄደ።

4 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተገናኘው፤ በለዓምም፣ “እነሆ፤ ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጅቻለሁ፤ በእያንዳንዱም ላይ አንድ ኮርማና አንድ አውራ በግ አቅርቤአለሁ” አለው።

5 እግዚአብሔርም (ያህዌ) በበለዓም አፍ መልእክት አስቀምጦ፣ “ወደ ባላቅ ተመልሰህ ይህን መልእክት ንገረው” አለው።

6 እርሱም ተመልሶ ሲሄድ ባላቅን ከመላው የሞዓብ አለቆች ጋር በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አገኘው።

7 ከዚያም በለዓም ንግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ፤“ባላቅ ከአራም አመጣኝ፣የሞዓብ ንጉሥ ከምሥራቅ ተራሮች።‘ና ያዕቆብን ርገምልኝ፤መጥተህም እስራኤልን አውግዝልኝ’ አለኝ።