1 ሙሴ ለእስራኤል የነገድ አለቆች እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤
2 አንድ ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ስእለት በሚሳልበት ወይም አንድ ነገር ለማድረግ በመሐላ ራሱን ግዴታ ውስጥ በሚያስገባበት ጊዜ ቃሉን ሳያጥፍ ያለውን ሁሉ መፈጸም አለበት።
3 “በአባቷ ቤት የምትኖር ሴት ልጅ ለእግዚአብሔር (ለያህዌ) ስእለት ብትሳል ወይም አንድ ነገር ለማድረግ በመሐላ ራሷን ግዴታ ውስጥ ብታስገባ፣
4 አባቷም መሳሏን ወይም ራሷን ግዴታ ውስጥ ማስገባቷን ሰምቶ ምንም ነገር ሳይላት ቢቀር፣ ስእለቶቿ በሙሉ፣ ራሷንም ግዴታ ውስጥ ያስገባችባቸው ነገሮች ሁሉ መፈጸም ይኖርባቸዋል።
5 አባቷ ይህንኑ ሰምቶ ከከለከላት ግን የትኛውም ስእለቷ ወይም ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችበት መሐላ አይያዝባትም፤ የከለከላት አባቷ ስለ ሆነ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነጻ ያደርጋታል።
6 “እንዲሁም ከተሳለች ወይም አምልጦአት ተናግራ ራሷን ግዴታ ውስጥ ካስገባች በኋላ ባል ብታገባ፣