ዘኁልቍ 36:3-9 NASV

3 ከሌሎች የእስራኤል ነገዶች ባል ቢያገቡ ድርሻቸው ከእኛ የዘር ርስት ላይ ተወስዶ የሚያገቧቸው ሰዎች ላሉበት ነገድ ይተላለፋል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ በዕጣ ከተደለደለልን ርስት ላይ ከፊሉ ሊቀነስብን ነው።

4 የእስራኤላውያን ዓመተ ኢዮቤልዩ በሚመጣበት ጊዜ የእነርሱ ድርሻ ወደ ባሎቻቸው ነገድ ይጨመራል፤ ይህ ከሆነም ድርሻቸው ከአባቶቻችን ነገድ ርስት ላይ ይወሰዳል።”

5 ከዚህ በኋላ ሙሴ እግዚአብሔር (ያህዌ) በተናገረው መሠረት እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “የዮሴፍ ነገድ የተናገረው ትክክል ነው፤

6 እንግዲህ የሰለጰዓድን ሴት ልጆች በተመለከተ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያዘው ይህ ነው፤ ከአባታቸው ነገድ ወገን እስከ ሆነ ድረስ የወደዱትን ማግባት ይችላሉ።

7 እያንዳንዱ እስራኤላዊም ከቀደሙት አባቶቹ በወረሰው ርስት ይጽና፤ በእስራኤል ከአንዱ ነገድ ወደ ሌላው ነገድ የሚተላለፍ ርስት አይኖርም።

8 እያንዳንዱ እስራኤላዊ የየአባቶቹን ርስት መውረስ ስላለበት፣ በማንኛውም የእስራኤል ነገድ ውስጥ ርስት የምትወርስ የትኛዪቱም ሴት፣ ከአባቷ ነገድ ወገን የሆነውን አንዱን ማግባት አለባት።

9 እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ የወረሰውን መሬት እንዳለ ማቈየት ስላለበት፣ ርስት ከአንዱ ነገድ ወደ ሌላው ነገድ አይተላለፍም።”