ዘኁልቍ 8:11-17 NASV

11 ከዚያም አሮን ሌዋውያኑን የእግዚአብሔርን (ያህዌ) አገልግሎት ለማከናወን ዝግጁ እንዲሆኑ ከእስራኤላውያን መካከል እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርባቸው።

12 “ሌዋውያኑ እጃቸውን በወይፈኖቹ ራስ ላይ ከጫኑ በኋላ ለሌዋውያኑ ማስተስረያ ይሆኑ ዘንድ የኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርባቸው።

13 ከዚያም ሌዋውያኑን በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፤ እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርባቸው።

14 በዚህ መሠረት ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን ትለያቸዋለህ፤ እነርሱም የእኔ ይሆናሉ።

15 “ሌዋውያኑን ካነጻሐቸውና እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገህ ካቀረብሀቸው በኋላ አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ወደ መገናኛው ድንኳን ይመጣሉ፤

16 እነርሱም ሙሉ በሙሉ የእኔ እንዲሆኑ የተሰጡኝ እስራኤላውያን ናቸው፤ ከማንኛዪቱም እስራኤላዊት በተወለደ በኵር ወንድ ልጅ ምትክ የራሴ እንዲሆኑ ወስጃቸዋለሁ።

17 ከሰውም ሆነ ከእንስሳ በእስራኤል የተወለደ ማንኛውም በኵር ተባዕት የእኔ ነው፤ በግብፅ የነበረውን በኵር ሁሉ በመታሁ ጊዜ የእኔ እንዲሆኑ ለይቻቸዋለሁ።