ዘፀአት 33:7-13 NASV

7 ሙሴ “የመገናኛው ድንኳን” ብሎ የጠራውን በመውሰድ፣ ከሰፈሩ ውጭ ራቅ ባለ ቦታ ላይ ይተክለው ነበር። እግዚአብሔርን (ያህዌ) መጠየቅ የሚፈልግ ሁሉ ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይሄድ ነበር።

8 ሙሴ ወደ ድንኳኑ በወጣ ጊዜ ሕዝቡ በመነሣት ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቁመው ይጠባበቁ ነበር።

9 ሙሴ ወደ ድንኳኑ ገብቶ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከሙሴ ጋር እየተነጋገረ ሳለ የደመናው ዐምድ ወርዶ በመግቢያው ላይ ይቆም ነበር።

10 ሕዝቡ የደመናውን ዓምድ በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆሞ ሲያዩት ሁሉም በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ይሰግዱ ነበር።

11 ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር እግዚአብሔር (ያህዌ) ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር፤ ከዚያም ሙሴ ወደ ሰፈሩ ይመለሳል፤ ረዳቱ የነበረው ብላቴናው የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ከድንኳኑ አይለይም ነበር።

12 ሙሴ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አለው፤ “ ‘እነዚህን ሕዝብ ምራ’ ብለህ ነግረኸኝ ነበር፤ ከእኔ ጋር የምትልከው ማን እንደሆነ ግን አላሳወቅኸኝም፤ ‘አንተን በስም አውቅሃለሁ፤ በፊቴም ሞገስ አግኝተሃል’ ብለህ ነበር።

13 በእኔ ደስ ተሰኝተህ ከሆነ፣ አንተን ዐውቅህና ያለ ማቋረጥ በፊትህ ሞገስ አገኝ ዘንድ መንገድህን አስተምረኝ፤ ይህ ሕዝብ የአንተ ሕዝብ መሆኑን አስታውስ።”