ሉቃስ

ምዕራፎች 8:27-33

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

27ኢየሱስ ከጀልባዋ ወደ ምድር በወረደ ጊዜ፣ አጋንንት ያደረበት አንድ ሰው ከከተማ ወጥቶ አገኘው፤ ይህ ሰው ለብዙ ጊዜ ልብስ ሳይለብስ፣ በቤትም ሳይኖር የመቃብርን ስፍራ ቤቱ ያደረገ ነበር። 28ኢየሱስንም ባየው ጊዜ እየጮኸ ፊቱ ተደፋ፤ በታላቅ ድምፅም፣ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ጋር ምን ጒዳይ አለህ? እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ” አለ። 29ርኩሱ መንፈስ ይህን ያለው ከሰውየው እንዲወጣ ኢየሱስ አዞት ስለ ነበር ነው። ርኩሱ መንፈስ በየጊዜው ስለሚነሣበት ሰውየው በሰንሰለትና በእግር ብረት እየታሰረ ቢጠበቅም የታሰረበትን ሰንሰለት እየበጣጠሰ ያደረበት ጋኔን ወደ በረሓ ይነዳው ነበር። 30ኢየሱስም፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው።እርሱም ብዙ አጋንንት ገብተውበት ስለ ነበር፣ “ሌጌዎን” አለው። 31አጋንንቱም እንጦርጦስ ግቡ ብሎ እንዳያዛቸውም አጥብቀው ለመኑት። 32በዚያም አካባቢ በተራራ ወገብ ላይ የብዙ ዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ አጋንንቱም ወደ ዐሣማው መንጋ ግቡ ብሎ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ እርሱም ፈቀደላቸው። 33አጋንንቱም ከሰውየው ወጥተው ወደ ዐሣማዎቹ ገቡ፤ የዐሣማውም መንጋ በገደሉ አፋፍ ቊልቊል በመንደርደር ባሕሩ ውስጥ ገብቶ ሰጠመ።