5 ምድር በሕዝቧ ትረክሳለች፤ሕግን ጥሰዋል፤ሥርዐትን ተላልፈዋል፤ዘላለማዊውንም ኪዳን አፍርሰዋል።
6 ስለዚህ ርግማን ምድርን ትበላለች፤ሕዝቦቿም ስለ በደላቸው ይቀጣሉ፤ስለዚህ የምድር ነዋሪዎች ተቃጥለዋል፤በጣም ጥቂት የሆኑት ቀርተዋል።
7 አዲሱ የወይን ጠጅ አለቀ፤ የወይኑም ተክል ደረቀ፤ደስተኞችም ሁሉ አቃሰቱ።
8 የከበሮ ደስታ ጸጥ አለ፤የጨፋሪዎች ጩኸት አበቃ፤ደስ የሚያሰኘውም በገና እረጭ አለ።
9 ከእንግዲህ እየዘፈኑ የወይን ጠጅ አይጠጡም፤መጠጡም ለሚጠጡት ይመራል።
10 የፈራረሰችው ከተማ ባድማ ሆነች፤የየቤቱም መግቢያ ተዘጋ።
11 በየአደባባዩ የወይን ጠጅ ያለህ እያሉ ይጮኻሉ፤ደስታው ሁሉ ወደ ሐዘን ይለወጣል፤ሐሤቱም ሁሉ ከምድር ገጽ ጠፍቶአል።