ኢሳይያስ 33 NASV

የጭንቅ ጊዜና ርዳታ

1 አንተ ሳትጠፋ የምታጠፋ፣አንት አጥፊ፣ ወዮልህ!አንተ ሳትካድ የምትክድ፣አንት ከዳተኛ፣ ወዮልህ!ማጥፋትን በተውህ ጊዜ፣ትጠፋለህ፤ክሕደትህንም በተውህ ጊዜ ትከዳለህ።

2 እግዚአብሔር ሆይ፤ ማረን፤አንተን ተስፋ አድርገናል።በየማለዳው ብርታት፣በጭንቅ ጊዜም ድነት ሁነን።

3 ሕዝቦች በድምፅህ ነጐድጓድ ይሸሻሉ፣መንግሥታት ስትነሣ ይበተናሉ።

4 ሕዝቦች ሆይ፤ አንበጣ እንደሚሰበስብ ብዝበዛችሁም ይሰበሰባል፤ሰዎችም እንደ ኩብኩባ ይጨፍሩበታል።

5 እግዚአብሔር በአርያም ተቀምጦአልና ከፍ ከፍ አለ፤ጽዮንን በጽድቅና በፍትሕ ይሞላታል።

6 እርሱ ለዘመንህ የሚያስተማምን መሠረት፣የድነት፣ የዕውቀትና የጥበብ መዝገብ ይሆናል፤ እግዚአብሔርንም መፍራት የዚህ ሀብት ቍልፍ ነው።

7 እነሆ፤ ጐበዞቻቸው በየመንገዱ ይጮኻሉ፤የሰላም መልእክተኞችም አምርረው ያለቅሳሉ።

8 አውራ ጐዳናዎች ባዶ ናቸው፤በመንገድ ላይ ሰው የለም፤ስምምነቱ ፈርሶአል፤መካሪዎቹ ተንቀዋል፤የሚከበርም የለም።

9 ምድሪቱ አለቀሰች፤ መነመነች፤ሊባኖስ ዐፈረች፤ ጠወለገች፤ሳሮን እንደ ዐረባ ምድረ በዳ ሆነች፤ባሳንና ቀርሜሎስ ቅጠላቸውን አረገፉ።

10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አሁን እነሣለሁ፤አሁን ከፍ ከፍ እላለሁ፤አሁን እከብራለሁ።

11 ገለባን ፀነሳችሁ፤እብቅንም ወለዳችሁ፤እስትንፋሳችሁም የሚበላችሁ እሳት ነው።

12 ሕዝቦች ኖራ እንደሚወጣው ድንጋይ ይቃጠላሉ፤እንደ እሾኽ ቍጥቋጦ በእሳት ይጋያሉ።”

13 እናንት በሩቅ ያላችሁ ያደረግሁትን ስሙ፤እናንት በቅርብ ያላችሁ ኀይሌን ዕወቁ!

14 በጽዮን ያሉ ኀጢአተኞች ደነገጡ፤አምላክ የሌላቸውም ፍርሀት ይዞአቸው፣“ከእኛ መካከል ከሚባላ እሳት ጋር ማን መኖር ይችላል፣ከዘላለም እሳትስ ጋር ማን መኖር ይችላል?” አሉ።

15 በጽድቅ የሚራመድ፣ቅን ነገር የሚናገር፣በሽንገላ የሚገኝ ትርፍ የሚንቅ፣መማለጃን ላለመቀበል እጁን የሚሰበሰብ፣የግድያን ሤራ ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን፣ክፋትን ላለማየት ዐይኑን የሚጨፍን፣

16 ይህ ሰው በከፍታ ላይ ይኖራል፤የተራራም ምሽግ መጠጊያው ይሆናል፤እንጀራ ይሰጠዋል፣ውሃውም አይቋረጥበትም።

17 ዐይኖችህ ንጉሡን በውበቱ ያዩታል፤በሩቅ የተዘረጋችውንም ምድር ይመለከታሉ።

18 የቀደመው መከራ ትዝ እያለህ፣“ያ ዋና አለቃ የት አለ?ግብር ተቀባዩስ ወዴት ሄደ?የመጠበቂያ ማማ ኀላፊውስ የት አለ?” ትላለህ።

19 እነዚያ ንግግራቸው የማይገባ፣የሚሉትም የማይታወቅ፣ሊረዱት የማይቻል ቋንቋ የሚናገሩትን ጋጠወጥ ሕዝብ ከእንግዲህ አታያቸውም።

20 በዓላታችንን የምናከብርባትን ከተማ ጽዮንን ተመልከት፤ሰላማዊ መኖሪያ፣ የማትነቃነቅ ድንኳን የሆነችውን፣ካስማዋ የማይነቀል፣ከገመዷ አንዱ እንኳ የማይበጠሰውን፣ኢየሩሳሌምን ዐይኖችህ ያያሉ።

21 እግዚአብሔር በዚያ ኀይላችን ይሆናል፤ባለ መቅዘፊያ ጀልባዎች እንደማያል ፉባቸው፣ታላላቅ መርከቦችም እንደማይሻገሯቸው፣ሰፋፊ ወንዞችና ጅረቶች ይሆንልናል።

22 እግዚአብሔር ዳኛችን ነው፤ እግዚአብሔር ሕግ ሰጪያችን ነው፤ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው፤የሚያድነንም እርሱ ነውና።

23 መወጠሪያ ገመድህ ላልቶአል፤ምሰሶው ጠብቆ አልተተከለም፤ሸራው አልተወጠረም፤በዚያ ጊዜ ታላቅ ምርኮ ይከፋፈላል፤አንካሳ እንኳ ሳይቀር ምርኮ ይወስዳል።

24 በጽዮን ተቀምጦ፣ “ታምሜአለሁ” የሚል አይኖርም፤በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ኀጢአትም ይቅር ይባላል።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50 51 52 53 54 55 56 57 58 59 60 61 62 63 64 65 66