1 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ትልቅ ሰሌዳ ወስደህ፣ ‘ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ’ ብለህ በተለመደው በሰው ፊደል ጻፍበት።
2 እኔም፣ ካህኑን ኡሪያንንና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ታማኝ ምስክሮቼ እንዲሆኑ እጠራቸዋለሁ።”
3 እኔም ወደ ነቢዪቱ ሄድሁ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። እግዚአብሔርም፣ እንዲህ አለኝ፤ “ስሙን ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ ብለህ ጥራው።
4 ሕፃኑም፣ ‘አባባ’ ወይም ‘እማማ’ ብሎ መጥራት ከመቻሉ በፊት፣ የደማስቆ ሀብትና የሰማርያ ምርኮ በአሦር ንጉሥ ይወሰዳል።”
5 እግዚአብሔርም እንደ ገና እንዲህ ሲል ተናገረኝ፤
6 “ይህ ሕዝብ በጸጥታ የሚፈሰውንየሰሊሆምን ውሆች ትቶ፣በረአሶንናበሮሜልዩ ልጅ ተደስቶአልና።
7 ስለዚህ ጌታ ታላቁንና ብርቱውንየጐርፍ ውሃ፣የአሦርን ንጉሥ ከነግርማ ሞገሱ ሁሉ ያመጣባቸዋል።ውሃውም ከቦዩ ዐልፎ ተርፎበወንዙ ዳር ያለውን ምድር ሁሉ ያጥለቀልቃል፤
8 እየጠራረገ ወደ ይሁዳ ይወርዳል፤እያጥለቀለቀ ያልፋል፤እስከ ዐንገትም ይደርሳል፤አማኑኤል ሆይ፤የተዘረጉ ክንፎቹ ምድርህን ከዳር እስከዳር ይሸፍናሉ።”
9 እናንተ አሕዛብ፣ ፎክሩ፤ግን ደንግጡ።በሩቅ አገር ያላችሁ አድምጡ፤ለጦርነትም ተዘጋጁ፤ ነገር ግን ደንግጡ፤ለጦርነትም ተዘጋጁ፤ ነገር ግን ደንግጡ፤
10 ተመካከሩ፤ ግን አይሳካም፤ዕቅድ አውጡ፤ ሆኖም አይጸናም፤እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና።
11 እግዚአብሔር ብርቱ እጁን በላዬ አድርጎ የእነዚህን ሰዎች መንገድ እንዳልከተል አስጠነቀቀኝ፤ እንዲህም አለኝ፤
12 “እነዚህ ሰዎች፣ ‘አድማ’ ብለው የሚጠሩትን፣ማንኛውንም ነገር፣ ‘አድማ’ አትበሉ፤እነርሱ የሚፈሩትን አትፍሩ፤አትሸበሩለትም።
13 ልትቀድሱ የሚገባው የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ብቻ ነው፤ልትፈሩት የሚገባው እርሱን ነው፤ልትንቀጠቀጡለት የሚገባውም እርሱ ነው።
14 እርሱም መቅደስ ይሆናል፤ለሁለቱ የእስራኤል ቤት ግንየሚያደናቅፍ ድንጋይየሚያሰናክልም ዐለት ይሆንባቸዋል፤ለኢየሩሳሌም ሕዝብምወጥመድና አሽክላ ይሆናል።
15 ከእነርሱ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ይወድቃሉ፤ ይሰበራሉ፤ወጥመድ ይገባሉ፤ ይያዛሉም።”
16 ምስክርነቱን አሽገው፤ሕጉንም በደቀ መዛሙርቴ መካከል አትመው።
17 ፊቱን ከያዕቆብ ቤት የሸሸገውን እግዚአብሔርን እጠብቃለሁ፤እርሱንም ተስፋ አደርጋለሁ።
18 እነሆ፤ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሰራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ለእስራኤል ምልክትና ድንቅ ነን።
19 ሰዎች፣ “የሚያነበንቡትንና የሚያሾካ ሹኩትን ሟርተኞችንና መናፍስት ጠሪዎችን ጠይቁ ቢሏችሁ፣ ሕዝቡ አምላኩን መጠየቅ አይገባውምን? በሕያዋን ምትክ ሙታንን መጠየቅ ለምን አስፈለገ?
20 ወደ ሕጉና ወደ ምስክር ቃሉ ሂዱ! እነርሱም እንዲህ ያለውን ቃል ባይናገሩ የንጋት ብርሃን አይበራላቸውም።
21 ተጨንቀውና ተርበው በምድሪቱ ላይ ይንከራተታሉ፤ ክፉኛ ሲራቡም ይቈጣሉ፤ ወደ ላይ እየተመለከቱ ንጉሣቸውንና አምላካቸውን ይራገማሉ።
22 ከዚያም ወደ ምድር ይመለከታሉ፣ የሚያዩትም ጭንቀት፣ ጨለማና የሚያስፈራም ጭጋግ ብቻ ነው፤ ወደ ድቅድቅ ጨለማም ይጣላሉ።