ኢሳይያስ 37 NASV

የኢየሩሳሌም ዐርነት ታወጀ

1 ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን ሲሰማ፣ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለበሰ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገባ።

2 የቤተ መንግሥቱን አስተዳዳሪ ኤልያቄምንና ጸሓፊውን ሳምናስን እንዲሁም ከካህናቱ ዋና ዋናዎቹን ማቅ ለብሰው ሁሉም ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ላካቸው።

3 እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፤ ይህ ቀን የጭንቀት፣ የተግሣጽና የውርደት ቀን ነው፤ ሕፃናት ሊወለዱ ሲሉ ብርታት እንደሚታጣበት ቀን ሆኖአል።

4 ሕያው አምላክን ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የጦር አዛዡን ቃል እግዚአብሔር አምላክህ ይሰማ ይሆናል፤ እግዚአብሔር አምላክህም ሰምቶ ይገሥጸው ይሆናል፤ ስለዚህ አንተም በሕይወት ለተረፉት ቅሬታዎች ጸልይ።”

5 የንጉሡ የሕዝቅያስ መልእክተኞች ወደ ኢሳይያስ መጡ፤

6 ኢሳይያስም እንዲህ አላቸው፤ “ጌታችሁን እንዲህ በሉት፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች እኔን ስለ ሰደቡኝ፣ በሰማኸው ቃል አትሸበር።

7 እነሆ፤ በላዩ መንፈስን እሰዳለሁ፤ ወሬም ሰምቶ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ በገዛ አገሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።’ ”

8 የጦር አዛዡም፣ የአሦር ንጉሥ ለኪሶን ለቆ መሄዱን ሲሰማ፣ ከነበረበት ተመለሰ፤ ንጉሡም የልብናን ከተማ ሲወጋ አገኘው።

9 ደግሞም ሰናክሬም፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊወጋው መምጣቱን ሰማ፤ ይህንንም እንደ ሰማ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞች ላከ፤ እንዲህም አለ፤

10 “ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት፤ ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ አትያዝም’ ብሎ የተማመንህበት አምላክ አያታልህ።

11 እነሆ፤ የአሦር ነገሥታት በአገሮች ሁሉ ላይ ያደረጉትን፣ ፈጽሞም እንዳጠፏቸው ሰምተሃል፤ አንተስ የምታመልጥ ይመስልሃልን?

12 የቀደሙት አባቶቼ ያጠፏቸውን፣ የጎዛንን፣ የካራንን፣ የራፊስን እንዲሁም በተላሳር የሚኖሩ የዔድንን ሰዎች የአሕዛብ አማልክት አድነዋቸዋልን?

13 የሐማት ንጉሥ፣ የአርፋድ ንጉሥ፣ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፣ የሄና ንጉሥ ወይም የዒዋ ንጉሥ የት አሉ?”

የሕዝቅያስ ጸሎት

14 ሕዝቅያስ ደብዳቤውን ከመልእክተኞቹ ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጥቶም ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው።

15 ሕዝቅያስም እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤

16 “በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር ባሉ መንግሥታት ሁሉ ላይ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርንም ፈጥረሃል።

17 አቤቱ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብል፤ አድምጥም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይኖችህን ክፈት፤ ተመልከትም። ሰናክሬም ሕያው አምላክን ለመሳደብ የላከውን ቃል ስማ።

18 “እግዚአብሔር ሆይ፤ በርግጥ የአሦር ነገሥታት እነዚህን ሕዝቦች፣ ምድራቸውንም ሁሉ ባድማ አድርገዋል።

19 አማልክታቸውን ወደ እሳት ጥለዋል፤ በሰው እጅ የተቀረጹ የድንጋይና የዕንጨት ምስሎች እንጂ አማልክት አልነበሩምና።

20 አሁንም፣ እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ እንደሆንህ ያውቁ ዘንድ፣ አቤቱ ከእጁ አድነን።”

የሰናክሬም ውድቀት

21 ከዚህ በኋላ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ሕዝቅያስ ላከ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ አሦር ንጉሥ፣ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ ጸልየሃልና፣

22 እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤“ ‘ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ፣ንቃሃለች፣ አፊዛብሃለች፤የኢየሩሳሌም ልጅ፣አንተ ስትሸሽ ራሷን ነቅንቃብሃለች።

23 የሰደብኸውና ያቃለልኸው ማንን ነው?ድምፅህንስ ከፍ ከፍ ያደረግኸው፣ዐይንህን በትዕቢት ያነሣኸው በማን ላይ ነው?በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው እኮ!

24 በመልእክተኞችህ በኩል፣በጌታ ላይ ብዙ የስድብ ቃል ተናገርህ፤እንዲህም አልህ፤“በሰረገሎቼ ብዛት፣የተራሮችንም ከፍታ፣የሊባኖስንም ጫፍ ወጥቻለሁ፤ረጃጅም ዝግባዎችን፣የተመረጡ ጥዶችን ቈርጫለሁ፤እጅግ ወደራቁት ከፍታዎች፣እጅግ ውብ ወደ ሆኑትም ደኖች ደርሻለሁ፤

25 በባዕድ ምድር ጒድጓዶችን ቈፈርሁ፤ከዚያም ውሃ ጠጣሁ።የግብፅን ምንጮች ሁሉ፣በእግሬ ረግጬ አደረቅሁ።”

26 “ ‘ይህን ቀድሞ እንደ ወሰንሁት፣ጥንትም እንዳቀድሁት፣አልሰማህምን?አሁን ደግሞ እንዲፈጸም አደረግሁት፤አንተም የተመሸጉትን ከተሞች የድንጋይክምር አደረግሃቸው።

27 የሕዝቦቻቸው ኀይል ተሟጦአል፤ደንግጠዋል፤ ተዋርደዋልም፤በሜዳ እንዳሉ ዕፀዋት፣እንደ ለጋ ቡቃያ፣በሰገነት ላይ እንደ በቀለ ሣር፣በእንጭጩ ዋግ እንደ መታው ሆነዋል።

28 “ ‘እኔ ግን የት እንዳለህ፣መምጣት መሄድህ ምን ጊዜ እንደሆነ፣በእኔም ላይ እንዴት በቍጣ እንደም ትነሣሣ ዐውቃለሁ።

29 በእኔ ላይ በቍጣ ስለ ተነሣሣህ፣እብሪትህም ወደ ጆሮዬ ስለ ደረሰ፣በአፍንጫህ ስናጌን፣በአፍህ ልጓሜን አገባለሁ፤በመጣህበትም መንገድ እንድትመለስአደርግሃለሁ።’

30 “ሕዝቅያስ ሆይ፤ ይህ ምልክት ይሆንልሃል፤“በዚህ ዓመት የገቦውን፣በሚቀጥለው ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤በሦስተኛው ዓመት ግን ትዘራላችሁ፤ ታጭዳላችሁ፤ወይን ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ።

31 እንደ ገናም የይሁዳ ቤት ቅሬታ፣ሥሩን ወደ ታች ይሰዳል፤ ከላይም ፍሬ ያፈራል፤

32 ቅሬታ የሆኑት ከኢየሩሳሌም፣የተረፉትም ከጽዮን ተራራ ይመጣሉና፤የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅናትይህን ያደርጋል።

33 “ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤“ወደዚች ከተማ አይገባም፤ፍላጻ አይወረውርባትም፤ጋሻ አንግቦ አይመጣባትም፤በዐፈር ቍልልም አይከባትም።

34 በመጣበት መንገድ ይመለሳል፤ወደዚች ከተማም አይገባም”ይላል እግዚአብሔር።

35 “ስለ ራሴና፣ ስለ አገልጋዬም ስለ ዳዊት፣ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ፤ አድናታለሁም።”

36 ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፤ ከአሦራውያን ሰፈር አንድ መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰው ገደለ፤ በሰፈር ያሉት ማለዳ ሲነሡ፤ ቦታው ሬሳ በሬሳ ነበር።

37 ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም አመለጠ፤ ወደ ነነዌም ተመልሶ በዚያ ተቀመጠ።

38 ሰናክሬም በአምላኩ በናሳራክ ቤተ ጣዖት በሚሰግድበት ጊዜ፣ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፤ ከዚያም ወደ አራራት ምድር ኰበለሉ፤ ልጁም አስራዶን በምትኩ ነገሠ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50 51 52 53 54 55 56 57 58 59 60 61 62 63 64 65 66