1 ከዚህ በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ‘በምድረ በዳ በዓል እንዲያደርግልኝ ሕዝቤን ልቀቅ’ ይላል” አሉት።
2 ፈርዖንም “እንድታዘዘውና እስራኤልን እንድለቅለት ለመሆኑ ይህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ማነው?” እግዚአብሔርን (ያህዌ) አላውቅም፤ እስራኤልንም አለቅም” አለ።
3 እነርሱም፣ “የዕብራውያን አምላክ (ኤሎሂም) ለእኛ ተገልጦልናል፤ የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳው ተጒዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት እንድንሠዋ ፍቀድልን፤ አለዚያ ግን በመቅሠፍት ወይም በሰይፍ ይመታናል” አሉት።
4 የግብፅ ንጉሥም፣ “እናንተ ሙሴና አሮን፤ ለምንድ ነው ሕዝቡን ሥራ የምታስፈቱት! በሉ እናንተም ወደየሥራችሁ ተመለሱ”
5 ፈርዖንም፣ “እነሆ፤ አሁን የምድሪቱ ሕዝብ እጅግ ብዙ ነው፤ እናንተም እንዳይሠሩ እያደረጋችኋቸው ነው” አለ።
6 በዚያኑ ዕለት ፈርዖን ለባሪያ ተቈጣጣሪዎቹና ለሕዝቡ አለቆች እንዲህ ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤
7 “ለጡብ ሥራ የሚያስፈልጋቸውን ጭድ ካለበት ቦታ ሄደው ራሳቸው ያምጡ እንጂ ከእንግዲህ እናንተ እንዳታቀርቡላቸው።
8 ሆኖም ቀድሞ በሚያቀርቡት ሸክላ ልክ ሠርተው እንዲያቀርቡ አድርጓቸው። የሥራ ድርሻቸውን አትቀንሱ። ሰነፎች ናቸው፤ ‘ሄደን ለአምላካችን መሥዋዕት እንሠዋ’ የሚሉትም ለዚህ ነው።
9 ለሐሰት ወሬ ስፍራ ሳይሰጡ ተግተው እንዲሠሩ ሥራውን አክብዱባቸው።”
10 ከዚያም የባሪያ ተቈጣጣሪዎቹና አለቆቹ ወጥተው ለሕዝቡ፦ “ፈርዖን የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእንግዲህ ጭድ አልሰጣችሁም፤
11 ሂዱና የራሳችሁን ጭድ ከየትም ፈልጋችሁ አምጡ፤ የሥራ ድርሻችሁ ግን ከቶ አይቀነስም’ ” አሉ።
12 ስለዚህም ሕዝቡ በጭድ ፈንታ ገለባ ለመሰብሰብ በግብፅ ምድር ሁሉ ተሰማሩ።
13 የባሪያ ተቈጣጣሪዎቹም “በየዕለቱ መሥራት የሚገባችሁ ሥራ ቀድሞ ጭድ ስናቀር ብላችሁ ከምትሠሩት ሥራ ማነስ የለበትም” እያሉ ያጣድፏቸው ነበር።
14 የሥራው የቅርብ ኀላፊዎች ተደርገው በፈርዖን የባሪያ ተቈጣጣሪዎች የተመደቡት እስራኤላውያንም፣ “የትናንቱንም ሆነ የዛሬውን ሸክላ ሥራ ድርሻችሁን እንደ ቀድሞው ለምን አላሟላችሁም?” እየተባሉ ይጠየቁና ይገረፉ ነበር።
15 ከዚያም ሥራውን በቅርብ ሆነው የሚቈጣጠሩት እስራኤላውያን ኀላፊዎች ፈርዖን ፊት ቀርበው እንዲህ ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ፤ “እኛን ባሮችህን እንደዚህ የምታደርገን ለምንድን ነው?
16 ለእኛ ለባሮችህ ጭድ ሳያቀርቡልን ሸክላ ሥሩ ይሉናል፤ ጥፋቱ የገዛ ሰዎችህ ሆኖ ሳለ እኛ ባሮችህ ግን እንገረፋለን።”
17 ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ልግመኞች! እናንተ ልግመኞች! እየደጋገማችሁ እንሂድ ‘ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እንሠዋ’ የምትሉት ለዚህ ነው።
18 በሉ አሁንም ወደ ሥራችሁ ተመለሱ፤ ምንም ጭድ አይሰጣችሁም፤ ያም ሆኖ ግን የተመደበላችሁን ሸክላ ማምረት አለባችሁ።”
19 እስራኤላውያን ኀላፊዎችም፣ “በየቀኑ የምትሠሩት ሸክላ ቍጥሩ ቀድሞ ከሚሠራው ሸክላ ማነስ የለበትም” ተብሎ ሲነገራቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ተረዱት።
20 ከፈርዖን ዘንድ እንደ ተመለሱ ሲጠብቋቸው የነበሩትን ሙሴንና አሮንን አግኝተው፣
21 “እግዚአብሔር (ያህዌ) ይይላችሁ፤ ይፍረድባችሁም ፈርዖንና ሹማምንቱ እንዲጠየፉን አደረጋችሁ፤ እንዲገድሉን በእጃቸው ሰይፍ ሰጣችኋቸው” አሏቸው።
22 ሙሴም ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተመልሶ፦ “አቤቱ ጌታ (አዶናይ) ሆይ፤ በዚህ ሕዝብ ላይ መከራ ያመጣኸው ለምንድን ነው? የላክኽኝ ለዚሁ ነው?
23 በአንተ ስም እናገር ዘንድ ወደ ፈርዖን ከሄድሁበት ጊዜ ጀምሮ፣ እርሱ በዚህ ሕዝብ ላይ፣ አበሳ አምጥቶአል፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አልታደግኸውም” አለው።