13 ከዚያም ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሰራዊት ሶርያውያንን ለመውጋት ወደ ፊት ገሠገሠ፤ ሶርያውያንም ከፊቱ ሸሹ።
14 ሶርያውያን መሸሻቸውን አሞናውያን ባዩ ጊዜ፣ እነርሱም ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዪቱ ውስጥ ገቡ። ስለዚህም ኢዮአብ አሞናውያንን መውጋቱን አቁሞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
15 ሶርያውያን በእስራኤላውያን እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ፣ እንደ ገና ተሰባሰቡ።
16 አድርአዛር መልክተኞችን ሰዶ ከወንዙ ማዶ ያሉትን ሶርያውያን አስመጣ፤ እነርሱም በአድርአዛር ሰራዊት አዛዥ በሶባክ መሪነት ወደ ኤላም ሄዱ።
17 ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ፣ መላውን እስራኤልን ሰበሰበ፤ ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ ዔላም ሄደ። ሶርያውያንም ለጦርነት ተሰልፈው ዳዊትን በግንባር ገጠሙት፤
18 ይሁን እንጂ ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ሰባት መቶ ሠረገለኞችንና አርባ ሺህ እግረኛ ወታደሮች ገደለባቸው። እንዲሁም የሰራዊታቸውን አዛዥ ሶባክን አቍስሎት ስለ ነበር፣ እዚያው ሞተ።
19 በአድርአዛር ሥር የነበሩት ነገሥታት ሁሉ በእስራኤል መሸነፋቸውን ባዩ ጊዜ ከእስራኤላውያን ጋር ሰላም መሠረቱ፤ ተገዙላቸውም።ስለዚህም ሶርያውያን ከዚያ በኋላ አሞናውያንን መርዳት ፈሩ።