17 የዚያን ዕለቱ ጦርነት እጅግ ከባድ ነበር፤ አበኔርና የእስራኤል ሰዎች በዳዊት ሰዎች ድል ሆኑ።
18 ሦስቱ የጽሩያ ወንዶች ልጆች ኢዮአብ፣ አቢሳና አሣሄል እዚያው ነበሩ። አሣሄል እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ፤
19 ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሳይል አበኔርን ተከታተለው።
20 አበኔርም ወደ ኋላው ዘወር ብሎ በመመልከት፣ “አሣሄል! አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት።
21 ከዚያም አበኔር፣ “ወደ ቀኝህ ወይም ወደ ግራህ ዘወር በልና አንዱን ጒልማሳ ይዘህ መሣሪያውን ንጠቀው” አለው። አሣሄል ግን እርሱን መከታተሉን አልተወም ነበር።
22 እንደ ገናም አበኔር፣ “እኔን መከታተል ብትተው ይሻልሃል፤ እኔስ ለምን ከመሬት ጋር ላጣብቅህ? ከዚያስ የወንድምህን የኢዮአብን ፊት ቀና ብዬ እንዴት አያለሁ?” አለው።
23 አሣሄል ግን መከታተሉን አልተወም፤ ስለዚህ አበኔር በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፣ ጦሩም በጀርባው ዘልቆ ወጣ፤ አሣሄልም እዚያው ወደቀ፤ ወዲያው ሞተ። እያንዳንዱም አሣሄል ወድቆ ወደ ሞተበት ስፍራ ሲደርስ ይቆም ነበር።