9 ኢዮአብም ከፊትና ከኋላው ጦር እንደ ከበበው ባየ ጊዜ፣ በእስራኤል ጀግንነታቸው ከታወቀው ጥቂቶቹን መርጦ በሶርያውያን ግንባር አሰለፋቸው።
10 የቀሩትን ሰዎች ደግሞ በወንድሙ በአቢሳ ሥር መድቦ በአሞናውያን ግንባር አሰለፋቸው።
11 ኢዮአብም እንዲህ አለ፤ ሶርያውያን የሚያይሉብኝ ከሆነ አንተ መጥተህ ትረዳኛለህ፤ አሞናውያን የሚያይሉብህ ከሆነ እኔ መጥቼ እረዳሃለሁ።
12 እንግዲህ በርታ፤ ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች በጀግንነት እንዋጋ፤ እግዚአብሔርም በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግ።
13 ከዚያም ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሰራዊት ሶርያውያንን ለመውጋት ወደ ፊት ገሠገሠ፤ ሶርያውያንም ከፊቱ ሸሹ።
14 ሶርያውያን መሸሻቸውን አሞናውያን ባዩ ጊዜ፣ እነርሱም ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዪቱ ውስጥ ገቡ። ስለዚህም ኢዮአብ አሞናውያንን መውጋቱን አቁሞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
15 ሶርያውያን በእስራኤላውያን እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ፣ እንደ ገና ተሰባሰቡ።