2 ሳሙኤል 19:20-26 NASV

20 እኔ አገልጋይህ ኀጢአት መሥራቴን አውቃለሁና፤ ዛሬ ግን ጌታዬን ንጉሡን ለመቀበል ከዮሴፍ ቤት ሁሉ የመጀመሪያ ሆኜ እነሆ መጥቻለሁ።”

21 ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ፣ “ሳሚ በእግዚአብሔር የተቀባውን የረገመ ስለ ሆነ፣ መሞት አይገባውምን?” አለ።

22 ዳዊትም፣ “እናንት የጽሩያ ልጆች፣ እናንተንና እኔን ምን የሚያገናኘን ነገር አለ? ዛሬ ጠላት ሆናችሁኛል! ማንስ ቢሆን ዛሬ በእስራኤል ዘንድ ሰው መሞት አለበት? እኔ በእስራኤል ላይ ንጉሥ መሆኔን ያወቅሁበት ቀን አይደለምን?” ብሎ መለሰ።

23 ስለዚህ ንጉሡ ሳሚን፣ “አትሞትም” አለው፤ ይህንንም ንጉሡ በመሐላ አጸናለት።

24 የሳኦል ልጅ ሜምፊቦስቴም ንጉሡን ለመቀበል ወረደ። ንጉሡ ከተሰደደበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተመለሰበት ዕለት ድረስ ለእግሩ ተገቢውን ጥንቃቄ አላደረገም፤ ጢሙን አልተላጨም፤ ልብሱንም አላጠበም ነበር።

25 እርሱም ንጉሡን ለመቀበል ከኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፣ “ሜምፊቦስቴ፣ አብረኸኝ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።

26 እርሱም እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ ሽባ በመሆኔ፣ ‘ከንጉሡ ጋር መሄድ እንድችል አህያዬ ይጫንልኝና ልቀመጥበት’ ብዬ ነበር፤ ይሁን እንጂ አገልጋዬ ሲባ አታለለኝ።