2 ሳሙኤል 24:11-17 NASV

11 በማግስቱ ጠዋት ዳዊት ከመነሣቱ በፊት የእግዚአብሔር ቃል የዳዊት ባለ ራእይ ወደ ሆነው ወደ ነቢዩ ወደ ጋድ መጣ፤

12 እንዲህም አለው፤ “ሂድና ዳዊትን፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሦስት ነገሮችን ለምርጫ አቅርቤልሃለሁ፤ በአንተ ላይ አደርግብህ ዘንድ አንዱን ምረጥ’ በለው።”

13 ስለዚህም ጋድ ወደ ዳዊት ሄዶ፣ “በምድርህ የሦስት ዓመት ራብ ይምጣብህ? ወይስ ጠላቶችህ እያሳደዱህ ሦስት ወር ትሸሽ? ወይስ ደግሞ በምድርህ ላይ የሦስት ቀን ቸነፈር ይምጣ? እንግዲህ አሁን ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ አስበህበት ወስን” አለው።

14 ዳዊትም ጋድን፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ታላቅ ስለ ሆነ በእግዚአብሔር እጅ እንውደቅ፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ” አለው።

15 ስለዚህም እግዚአብሔር ከዚያች ዕለት ጥዋት አንሥቶ እስከ ተወሰነው ቀን ድረስ በእስራኤል ላይ ቸነፈር ላከ፤ በዚህም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሰባ ሺህ ሰው አለቀ።

16 የእግዚአብሔር መልአክ ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት እጁን በዘረጋ ጊዜ፣ የደረሰው ጒዳት እግዚአብሔርን ስላሳዘነው፣ ሕዝቡን የሚቀሥፈውን መልአክ “በቃ! እጅህን መልስ” አለው። በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር።

17 ዳዊት ሕዝቡን የሚቀሥፈውን መልአክ ባየ ጊዜ እግዚአብሔርን፣ “እነሆ ኀጢአት የሠራሁም የተሳሳትሁም እኔ ነኝ፤ እነዚህ ግን በጎች ናቸው፤ ምን አጠፉ? እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን” አለ።