6 ንጉሡና ሰዎቹ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን ለመውጋት ወደዚያ ሄዱ። ኢያቡሳውያንም፣ “ዳዊት እዚህ ሊገባ አይችልም” ብለው ስላሰቡ ዳዊትን፣ “ዕውሮችና አንካሶች እንኳ ይከለክሉሃልና ወደዚህች አትገባም” አሉት።
7 ይሁን እንጂ ዳዊት የጽዮንን ዐምባ ያዘ፤ ይህችም የዳዊት ከተማ የተባለችው ናት።
8 በዚያም ዕለት ዳዊት፣ “ኢያቡሳውያንን ድል ማድረግ የሚፈልግ፣ የዳዊት ጠላቶች ወደሚሆኑ፣ ‘አንካሶችና ዕውሮች’ ለመድረስ በውሃ መተላለፊያው ሽቅብ መውጣት አለበት” አለ። እንግዲህ፣ “ ‘አንካሶችና ዕውሮች’ ወደ ቤተ መንግሥት አይገቡም” ያሉት ለዚህ ነው።
9 ከዚያም ዳዊት መኖሪያውን በዐምባዪቱ ላይ አደረገ፤ የዳዊት ከተማም ብሎ ጠራት። ዳዊትም ከሚሎ አንሥቶ ወደ ውስጥ ዙሪያዋን ገነባት።
10 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር፣ ዳዊት ከዕለት ወደ ዕለት እየበረታ ሄደ።
11 በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ እንዲሁም የዝግባ ዕንጨት፣ አናጢዎችንና ድንጋይ ጠራቢዎችን አብሮ ሰደደ፤ እነርሱም ለዳዊት ቤተ መንግሥት ሠሩለት።
12 እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥነቱን እንዳጸናለት፣ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም መንግሥቱን እንዳሰፋለት ዳዊት ዐወቀ።