2 ሳሙኤል 9:1-7 NASV

1 ዳዊትም፣ “ስለ ዮናታን ስል ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው ይኖር ይሆን?” በማለት ጠየቀ።

2 በዚያን ጊዜ ከሳኦል ቤት ሲባ የሚባል አንድ አገልጋይ ስለ ነበር፣ ወደ ዳዊት እንዲሄድ ነገሩት። ንጉሡም፣ “ሲባ የምትባለው አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “አዎን እኔ አገልጋይህ ነኝ” አለ።

3 ንጉሡም፣ “የእግዚአብሔርን ቸርነት እንዳደርግለት ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው የለምን?” ሲል ጠየቀው።ሲባም ለንጉሡ፣ “እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ የዮናታን ልጅ አለ” ብሎ መለሰለት።

4 ንጉሡም፣ “የት ነው ያለው?” ብሎ ጠየቀ።ሲባም፣ “ሎዶባር በተባለ ስፍራ በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት ይገኛል” ብሎ መለሰለት።

5 ስለዚህም ንጉሥ ዳዊት፣ ሜምፊቦስቴን ከዓሚኤል ከማኪር ቤት ከሎደባር ልኮ አስመጣው።

6 የሳኦል ልጅ፣ የዮናታን ልጅ ሜምፊቦስቴ ወደ ዳዊት በመጣ ጊዜ፣ አክብሮቱን ለመግለጥ ለጥ ብሎ እጅ ነሣ።ዳዊትም፣ “ሜምፊቦስቴ” ብሎ ጠራው።እርሱም፣ “እነሆ፤ አገልጋይህ” አለ።

7 ዳዊትም፣ “አትፍራ፤ ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ስል በእርግጥ ቸርነት አደርግልሃለሁና። የአባትህን የሳኦልን ምድር በሙሉ እመልስልሃለሁ፤ ዘወትርም ከማዕዴ ትበላለህ” አለው።