መሳፍንት
ምዕራፎች 7:13-19
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
13አንድ ሰው ያየውን ሕልም ለጓደኛው በሚነግርበት ጊዜ ጌዴዎን እዚያ ደረሰ። ያም ሰው፣ “በሕልሜ ክብ የሆነ አንድ የገብስ ቂጣ ከላይ ተንከባሎ በምድያማውያን ሰፈር ላይ ሲወርድ፣ ድንኳኑንም ሲመታው ከአመታቱም ኀይለኛነት የተነሣ ድንኳኑ ተገልብጦ ሲፈራርስ አየሁ” በማለት ይነግረው ነበር።
14ጓደኛውም መልሶ፣ “ይህ የእስራኤላዊው የኢዮአስ ልጅ የጌዴዎን ሰይፍ እንጂ ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድያማውያንንና ሰፈሩን በሙሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶታልና” አለው።
15ጌዴዎንም ሕልሙንና ፍቺውን በሰማ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ ከዚያም ወደ እስራኤላውያን ሰፈር ወጥቶ፣ “እግዚአብሔር የምድያማውያንን ሰፈር በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተነሡ” አላቸው።
16ሦስቱን መቶ ሰዎች በሦስት ቡድን ከፍሎ፣ እያንዳንዱን ሰው ቀንደ መለከትና በውስጡ ችቦ ያለበት ባዶ ማሰሮ በእጁ እንዲይዝ አደረገ።
17ጌዴዎንም እንዲህ አላቸው፤ እኔን ተመልከቱ፤ የማደርገውንም አድርጉ፤ በሰፈሩ ዳርቻ ስደርስ እኔ የማደርገውን አይታችሁ ልክ እንደዚያው አድርጉ።
18እኔና አብረውኝ ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከቶቻችንን በምንነፋበት ጊዜ እናንተም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከቶቻቸሁን እየነፋችሁ፣ ‘ለእግዚአብሔርና ለጌዴዎን’ ብላችሁ ጩኹ።”
19ዘቦቹ ተቀያይረው የእኩለ ሌሊቱን ጥበቃ በጀመሩበት ጊዜ፣ ጌዴዎንና አብረውት የነበሩት መቶ ሰዎች በሰፈሩ ዳርቻ ደረሱ፤ እነርሱም ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ የያዟቸውንም ማሰሮች ሰበሩ።