ኢሳይያስ 30:24-30 NASV

24 የዕርሻ በሬዎችና አህዮች በመንሽና በላይዳ የተለየውን ገፈራና ድርቆሽ ይበላሉ።

25 በታላቁ የዕልቂት ቀን ምሽጎች ሲፈርሱ፣ በረጅም ተራራ ሁሉና ከፍ ባለውም ኰረብታ ሁሉ ላይ ወራጅ ወንዝ ይፈስሳል።

26 እግዚአብሔር የሕዝቡን ስብራት ሲጠግን፣ ያቈሰለውንም ሲፈውስ፣ ጨረቃ እንደ ፀሓይ ታበራለች፤ የፀሓይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት ዕጥፍ ይደምቃል።

27 እነሆ፤ የእግዚአብሔር ስም፣ከሚነድ ቍጣ፣ ጥቅጥቅ ካለና ከሚትጐለጐል የጢስ ደመና ጋር ከሩቅ ይመጣል፤ከንፈሮቹ ቍጣን የተሞሉ ናቸው፤ምላሱም የሚባላ እሳት ነው።

28 እስትንፋሱ እንደሚጠራርግ፣እስከ ዐንገት እንደሚደርስም የውሃ ሙላት ነው፤መንግሥታትን በጥፋት ወንፊት ያበጥራቸዋል፤በሕዝቦችም መንጋጋ፣መንገድ የሚያስት ልጓም ያስገባል።

29 በሌሊት የተቀደሰ በዓል ስታከብሩእንደምትዘምሩ፣ትዘምራላችሁ፤ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ወደ እስራኤል ዐለት፣ሰዎች ዋሽንት እየነፉ በደስታ እንደሚወጡ፣የእናንተም ልብ እንዲሁ ሐሤት ያደርጋል።

30 እግዚአብሔር በሚነድ ቍጣና በሚባላ እሳት፣በወጀብና በነጐድጓድ፣ በበረዶም ድንጋይ፣ግርማ የተሞላበትን ድምፁን ሰዎች እንዲሰሙ አድርጎ ያሰማል፤ክንዱም ስትወርድ ያሳያቸዋል።