1 “አንቺ የባቢሎን ድንግል ልጅ ሆይ፤ውረጂ፤ በትቢያ ላይ ተቀመጪ፤አንቺ የባቢሎናውያን ልጅ ሆይ፤ከዙፋንሽ ውረጂ፤ መሬት ላይ ተቀመጪ፤ከእንግዲህ ውብ ወይም ለግላጋ፣ተብለሽ አትጠሪም።
2 ወፍጮ ወስደሽ እህል ፍጪ፤መሸፋፈኛሽን አውልቂ፤ቀሚስሽንም ከፍ ከፍ አድርጊ፤ ባትሽን ግለጪ፤እየተንገዳገድሽ ወንዙን ተሻገሪ።
3 ዕርቃንሽ ይገለጥ፤ኀፍረትሽ ይታይ፤እበቀላለሁ፤እኔ ማንንም አልተውም።
4 የሚቤዠን የእስራኤል ቅዱስ፣ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
5 “አንቺ የባቢሎናውያን ልጅ ሆይ፤ወደ ጨለማ ግቢ፤ ዝም ብለሽም ተቀመጪ፤ከእንግዲህ የመንግሥታት እመቤት፣ተብለሽ አትጠሪም።
6 ሕዝቤን ተቈጥቼ ነበር፤ርስቴን አርክሼው ነበር፤አሳልፌ በእጅሽ ሰጠኋቸው፤አንቺ ግን አልራራሽላቸውም፤በዕድሜ በገፉት ላይ እንኳ፣እጅግ ከባድ ቀንበር ጫንሽባቸው።