ኢሳይያስ 56:3-9 NASV

3 ወደ እግዚአብሔር የተጠጋ መጻተኛ፣“እግዚአብሔር በርግጥ ከሕዝቡ ይለየኛል” አይበል፤ጃንደረባም፣“እኔ ደረቅ ዛፍ ነኝ” አይበል።

4 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ሰንበቶቼን ለሚያከብሩ ጃንደረቦች፣ደስ የሚያሰኘኝን ለሚመርጡ፣ቃል ኪዳኔን፣ ለሚጠብቁ

5 በቤተ መቅደሴና በቅጥሮቼ ውስጥ፣ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የበለጠ፣መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ለዘላለም፣የማይጠፋ ስም እሰጣቸዋለሁ።

6 እርሱን ለማገልገል፣ራሳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያቈራኙ መጻተኞች፣ የእግዚአብሔርን ስም በመውደድ፣እርሱንም በማምለክ፣ሰንበትን ሳያረክሱ የሚያከብሩትን ሁሉ፣ቃል ኪዳኔንም የሚጠብቁትን፣

7 ወደ ተቀደሰው ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤በጸሎት ቤቴም ውስጥ ደስ አሰኛቸዋለሁ።የሚቃጠል መሥዋዕታቸውንና ሌሎች መሥዋዕቶቻቸውን፣በመሠዊያዬ ቢሠዉ እቀበላቸዋለሁ፤ቤቴ፣ ለሕዝቦች ሁሉየጸሎት ቤት ተብሎ ይጠራልና።”

8 የተበተኑትን እስራኤል የሚሰበስብ፣ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ከተሰበሰቡት በተጨማሪ፣ሌሎችን እንደ ገና እሰበስባለሁ።”

9 እናንት የምድር አራዊት ሁሉ ኑ፤እናንት የዱር አራዊት ሁሉ ኑና በጥርሳቸሁ ቦጫጭቁ።