ኢሳይያስ 66:1-6 NASV

1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ምድርም የእግሬ ማረፊያ ናት፤ታዲያ የምትሠሩልኝ ቤት፣የማርፍበትስ ስፍራ የቱ ነው?

2 እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጄ አልሠራችምን?እንዲገኙስ ያደረግሁ እኔ አይደለሁምን?”ይላል እግዚአብሔር።“ነገር ግን እኔ ወደዚህ፣ትሑት ወደ ሆነና መንፈሱ ወደ ተሰበረ፣በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።

3 ነገር ግን ወይፈን የሚሰዋልኝ፣ሰው እንደሚገድል ነው፤የበግ ጠቦት የሚያቀርብልኝ፣የውሻ ዐንገት እንደሚሰብር ሰው ነው፤የእህል ቍርባን የሚያዘጋጅልኝ፣የዕሪያ ደም እንደሚያቀርብልኝ ሰው ነው፤የመታሰቢያን ዕጣን የሚያጥንልኝም፣ጣዖትን እንደሚያመልክ ሰው ነው፤የገዛ መንገዳቸውን መርጠዋል፤ነፍሳቸውም በርኵሰታቸው ደስ ይላታል።

4 ስለዚህ ችግር እንዲደርስባቸው አደርጋለሁ፤የፈሩትንም አመጣባቸዋለሁ፤በተጣራሁ ጊዜ የመለሰ፣በተናገርሁ ጊዜ ያደመጠ ሰው የለምና።በፊቴ ክፉ ነገር አደረጉ፤የሚያስከፋኝንም መረጡ።”

5 እናንት በቃሉ የምትንቀጠቀጡ፣ይህን የእግዚአብሔር ቃል ስሙ፤“እናንት ወንድሞቻችሁ የጠሏችሁ፣ስለ ስሜም አውጥተው የጣሏችሁ፣‘እስቲ እግዚአብሔር ይክበርና፣የእናንተን ደስታ እንይ’ አሏችሁ፤ይሁን እንጂ ማፈራቸው አይቀርም።

6 ያን የጩኸት ድምፅ ከከተማው ስሙ!ያን ጫጫታ ከቤተ መቅደሱ ስሙ!ይኸውም የእግዚአብሔር ድምፅ ነው፤ለጠላቶቹም የሚገባቸውን ሁሉ ይከፍላቸዋል።