3 ነገር ግን ወይፈን የሚሰዋልኝ፣ሰው እንደሚገድል ነው፤የበግ ጠቦት የሚያቀርብልኝ፣የውሻ ዐንገት እንደሚሰብር ሰው ነው፤የእህል ቍርባን የሚያዘጋጅልኝ፣የዕሪያ ደም እንደሚያቀርብልኝ ሰው ነው፤የመታሰቢያን ዕጣን የሚያጥንልኝም፣ጣዖትን እንደሚያመልክ ሰው ነው፤የገዛ መንገዳቸውን መርጠዋል፤ነፍሳቸውም በርኵሰታቸው ደስ ይላታል።
4 ስለዚህ ችግር እንዲደርስባቸው አደርጋለሁ፤የፈሩትንም አመጣባቸዋለሁ፤በተጣራሁ ጊዜ የመለሰ፣በተናገርሁ ጊዜ ያደመጠ ሰው የለምና።በፊቴ ክፉ ነገር አደረጉ፤የሚያስከፋኝንም መረጡ።”
5 እናንት በቃሉ የምትንቀጠቀጡ፣ይህን የእግዚአብሔር ቃል ስሙ፤“እናንት ወንድሞቻችሁ የጠሏችሁ፣ስለ ስሜም አውጥተው የጣሏችሁ፣‘እስቲ እግዚአብሔር ይክበርና፣የእናንተን ደስታ እንይ’ አሏችሁ፤ይሁን እንጂ ማፈራቸው አይቀርም።
6 ያን የጩኸት ድምፅ ከከተማው ስሙ!ያን ጫጫታ ከቤተ መቅደሱ ስሙ!ይኸውም የእግዚአብሔር ድምፅ ነው፤ለጠላቶቹም የሚገባቸውን ሁሉ ይከፍላቸዋል።
7 “ከማማጧ በፊት፣ትወልዳለች፤በምጥ ጣር ከመያዟ በፊት፣ወንድ ልጅ ትገላገላለች።
8 እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶ ያውቃል?እንዲህ ያለ ነገርስ ማን አይቶ ያውቃል?አገር በአንድ ጀምበር ይፈጠራልን?ወይስ ሕዝብ በቅጽበት ይገኛል?ጽዮንን ምጥ ገና ሲጀምራት፣ልጆቿን ወዲያውኑ ትወልዳለች።
9 ሊወለድ የተቃረበውን፣እንዳይወለድ አደርጋለሁን?” ይላል እግዚአብሔር።“በሚገላገሉበት ጊዜስ፣ማሕፀን እዘጋለሁን?” ይላል አምላክሽ።