1 የዖዝያን የልጅ ልጅ፣ የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ዘመን፣ የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፤ ነገር ግን ድል ሊያደርጓት አልቻሉም።
2 ለዳዊት ቤት፣ “ሶርያና ኤፍሬም ተባብረዋል” የሚል ወሬ በደረሰ ጊዜ፣ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ የአካዝና የሕዝቡ ልብ እንዲሁ ተናወጠ።
3 እግዚአብሔርም ኢሳይያስን እንዲህ አለው፤ “አንተና ልጅህ ሸአር ያሹብ አካዝን ለመገናኘት ወደ ልብስ አጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኵሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤
4 እንዲህም በለው፤ ‘ተጠንቀቅ፤ ተረጋጋ፤ አትፍራ በእነዚህ ከእሳት ተርፈው በሚጤሱት በሁለቱ የዕንጨት ጒማጆች፣ በሶርያና በንጉሥዋ በረአሶን እንዲሁም በሮሜልዩ ልጅ ቍጣ አትሸበር።
5 ሶርያ ኤፍሬምና፣ የሮሜልዩ ልጅ ሊያጠፉህ እንዲህ ብለው ተማከሩ፤
6 “ይሁዳን እንውረር፤ እንበታትነው ተከፋፍለንም እንግዛው፤ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥባት።”