12 እነዚህን የበኵራት ቊርባን አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ማቅረብ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን ሽታው ደስ የሚያሰኝ ቊርባን ሆነው በመሠዊያ ላይ ለመቃጠል አይቀርቡም።
13 የምታቀርበውን የእህል ቊርባን ሁሉ በጨው ቀምመው፤ የአምላክህ (ኤሎሂም) የቃል ኪዳን ጨው ከእህል ቊርባንህ አይታጣ፤ በቊርባንህም ላይ ጨው ጨምርበት።
14 “ ‘የእህል በኵራት ቊርባን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በምታመጣበት ጊዜ፣ የተፈተገና በእሳት የተጠበሰ እሸት አቅርብ።
15 ዘይት ጨምርበት፤ ዕጣንም በላዩ አስቀምጥ፤ ይህ የእህል ቊርባን ነው።
16 ካህኑም ከተፈተገው እህልና ከዘይቱ ወስዶ፣ ከዕጣኑ ሁሉ ጋር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ መታሰቢያ አድርጎ ያቃጥል።