22 “ ‘አንድ የሕዝብ መሪ ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ አምላኩም እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዛት አንዱን ተላልፎ ቢገኝ እርሱ በደለኛ ነው።
23 ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ እንከን የሌለበትን ተባዕት ፍየል የግሉ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ።
24 እጁንም በፍየሉ ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበትም ስፍራ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይረደው፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው።
25 ካህኑም ከመሥዋዕቱ ደም በጣቱ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ያፍሰው።
26 የኅብረት መሥዋዕቱን እንዳቃጠለ ሁሉ ሥቡንም በሙሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ በዚህም መሠረት ካህኑ የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰረይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።
27 “ ‘ከሕዝቡ መካከል አንዱ ሰው ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዛት አንዱን ተላልፎ ቢገኝ እርሱ በደለኛ ነው።
28 ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ፣ እንከን የሌለባትን እንስት ፍየል ስለ ፈጸመው ኀጢአት የግሉ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ።