ዘሌዋውያን 4:6-12 NASV

6 ጣቱንም በደሙ ውስጥ ነክሮ ከመቅደሱ መጋረጃ ትይዩ፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው።

7 ካህኑ ከደሙ ጥቂት ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያለውንና ሽታው ጣፋጭ የሆነ ዕጣን የሚታጠንበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ። የተረፈውን የወይፈኑን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ ባለው በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ግርጌ ያፍሰው፤

8 ለኀጢአት መሥዋዕት ከሚቀርበው ወይፈን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ይኸውም፦ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብና ከሆድ ዕቃው ጋር የተያያዘውን ሥብ፣

9 ሁለቱንም ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም የጒበቱን መሸፈኛ ከኵላሊቶቹ ጋር አብሮ አውጥቶ ያቅርብ፤

10 ለኅብረት መሥዋዕት ከሚቀርበው ወይፈን እንዳወጣ ሁሉ ሥቡን ያውጣ፤ ካህኑም የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ያቃጥለው።

11 ነገር ግን የወይፈኑን ቈዳና ሥጋውን ሁሉ፣ ጭንቅላቱንና እግሮቹን፣ ሆድ ዕቃውንና ፈርሱን፣

12 የወይፈኑን ብልት ሁሉ ከሰፈር ውጭ ዐመድ ወደሚፈስበት በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ ወደ ሆነው ስፍራ ይውሰደው፤ በተቈለለው ዐመድ ላይ ዕንጨት አንድዶ ያቃጥለው።