ዘሌዋውያን 9:2-8 NASV

2 አሮንንም እንዲህ አለው፤ “የኀጢአት መሥዋዕት እንዲሆንልህ አንድ እንቦሳ እንዲሁም የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲሆንልህ አንድ አውራ በግ፣ ወስደህ፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቅርባቸው፤ ሁለቱም እንከን የሌለባቸው ይሁኑ።

3 እስራኤላውያንንም እንዲህ በላቸው፤ ‘ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት እንከን የሌለባቸውን የአንድ ዓመት እምቦሳና የአንድ ዓመት ጠቦት፣

4 ለኅብረት መሥዋዕት አንድ በሬና አንድ አውራ በግ በዘይት ከተለወሰ የእህል ቊርባን ጋር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለመሠዋት አቅርቡ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዛሬ ይገለጥላችኋልና።’ ”

5 እነርሱም ሙሴ ያዘዛቸውን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አመጡ፤ ሕዝቡም በሙሉ ቀርበው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቆሙ።

6 ሙሴም፣ “የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር ይገለጥላችሁ ዘንድ፣ እንድታደርጉት እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዛችሁ ይህ ነው” አለ።

7 ሙሴ አሮንን፣ ወደ መሠዊያው ቀርበህ የኀጢአት መሥዋዕትህንና የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን ሠዋ፤ ለራስህና ለሕዝቡም አስተሰርይ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት የሕዝቡን መሥዋዕት አቅርብ፤ አስተሰርይላቸውም” አለው።

8 አሮንም ወደ መሠዊያው መጥቶ ስለ ራሱ የኀጢአት መሥዋዕት የቀረበውን እምቦሳ ዐረደው።